
መግቢያ
በህብረተሰብ ታሪክ ውስጥ ስለ ሰብዓዊ መብቶች የመከበር አስፈላጊነት በግልጽ መወራትና መጻፍ የተጀመረው በቅርብ ጊዜ
ይሁን እንጂ፣ የሰው ልጅ በተፈጥሮው ጭቆናን የማይቀበል ግን ደግሞ በአቅም ማነስ ብቻ ለጉልበታሙ ይገዛ ነበር እንጂ፣
እንደ ሰው ማንም ከማን እንደማይበልጥና በተፈጥሮም ከአካልና የአዕምሮ ብስለት መበላለጥ ሌላ፣ ሰው በሰውነቱ እኩል
እንደሆነ ሁሉም ያምናል። ለምሳሌ በተለምዶ የሴት ልጅ እንደ ወንዶች ቀስትና ደጋን ይዛ ወጥታና አድና ቤተሰቡን መመገብ
አትችልም ተብሎ በወንዶች ስለተወሰነባቸውና ውሎአቸው ቤት ውስጥ መዋል፣ ልጆችን መንከባከብና ለቤተሰቡ ምግብ
ማብሰል ስለሆነ፣ በማህበረሰቡ ውስጥ ከሚደረገው ማንኛውም ውይይትና ውሳኔ ተገልለው ኖረዋል። ይህ ሰው ሰራሽ የሆነ
የሥራ ክፍፍል፣ በመብት ደረጃ ወንዶችን የበላይ አድርጎ ያስቀመጠና ለዘመናት በሥራ ላይ የዋለ ስለሆነ፣ ወንዶች ከሴቶች
የበለጠ መብት ቢኖራቸው “ተፈጥሮያዊ” ነው ብለን እስከማመን አድርሶን ነበር። ከሴቶች የነጻነት ትግል በኋላ ግን፣ ዛሬ በብዙ
አገራት ሴቶች በህብረተሰቡ ውስጥ የመሪነትን ቦታ ወስደው ከወንዶች በበለጠ እንጂ ባላነሰ መልኩ ተልዕኮያቸውን እየፈጸሙ
መገኘታቸው፣ ለዘመናት ሰፍኖ የነበረው የሴቶችን የበታችነት ያራመደው አስተሳሰብ፣ ለመጨቆን ሆን ተብሎ በወንዶች
የተጠነሰሰ እንጂ ተፈጥሮ ወንድንም ሴትንም እንደማያበላልጥና ወንዶች ከሴቶች የበለጠ ሰብዓዊ መብት እንደሌላቸው
አስመስክሯል።
ሰብዓዊ መብቶችና ተከታታይ መንግሥቶቻችን፣
ባገራችን ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፍ የኖረው የዜጎች ሰብዓዊ መብቶች ጥሰት፣ ከላይ የሴቶችን መብት አስመልክቼ
ለአብነት እንዳስቀመጥኩት፣ ሰው ሰራሽ መሆኑ ቀርቶ ተፈጥሮያዊ ነው ብለን እንድንቀበልና መብታችንም ሲጣስ
እንዳናጉረምርም በህግና በልምድ ተጠፍረን ገዢዎቻችን መብታችንን ሲረግጡ አሜን ብለን እንድንኖር ተገድደን ነበር። ዓፄ
ኃይለ ሥላሴ ካባታቸው ከራስ መኮንንና ከናታቸው ወይዘሮ የሺ ዓሊ በጋራ ሙለታ መወለዳቸውንና፣ ዓፄ ምኒልክ አልጋ
ወራሼ ብለው የሾሙትን ልጅ ኢያሱን፣ በሸዋ መኳንንት ብርታት አግልለውት መንገሳቸውን እያወቅን፣ ቤተ ክርስቲያን እንኳ
ተደምራ “የይሁዳ አንበሳ” “ሥዩመ እግዚአብሔር” ናቸው ብለን እንድናምን ተደረገ። እግዚአብሔር የሾመውን ደግሞ መብቴን
ጥሰሃል ብሎ መክሰስ ይቅርና ማሰብም ራሱ ኃጢአት ነው ተብሎ ስለሚታሰብ ህዝቡ ሰብዓዊ መብቶቹ እንኳ ሲጣሱ “እግዜርን
ላለማስቀየም” ብሎ ሰጥ ለጥ ብሎ ተገዛ። ህገ መንግሥት ሲደነገግም ንጉሥ በእግዚአብሄር ስለተሾመ ከህጎች ሁሉ በላይ የሆነና
የማይከሰስ በመሆኑ የደንቦቹ ተፈጻሚነት በሰፊው ህዝብ ላይ ብቻ መሆኑን አስተማሩን። ይህን ለዘመናት የተንሰራፋና
“የበላዮች” በጉልበት የጫኑብን ሚዛኑ የተዛባና የሰው ልጆችን ተፈጥሮያዊ እኩልነትን የማይቀበለው አሰራር ነው እንግዲህ
ተዋህዶን፣ ዛሬም ድረስ ትላልቅ ባለሥልጣናት ፊት ይቅርና የመንግሥት ግብር እንኳ ለመክፈል ተራ ግምጃ ቤት ኃላፊ ፊት
ስንቀርብ፣ ነጠላችንን አገልድመን፣ እጃችንን ወደ ኋላ አድርገንና ራሳችንን ዝቅ አድርገን የተወሰነብንን ከፍለን፣ ግብሩንም
ለመክፈል “ስለፈቀዱልን” አመስግነንና እጅ ነስተን ወደ ቤታችን የምንመለሰው።
ኢትዮጵያ የጥቁር አፍሪካ ብቸኛ መሥራች አባል የነበረችበት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ)፣ ገና እንደተመሰረተ
ያተኮረው በሰብዓዊ መብቶች መከበር ጉዳይ ላይ ነበር። ድርጅቱ በ 1948 ዓም የመጀመርያውን ዓለም ዓቀፋዊ የሰው ልጆች
መብት “ዓዋጅ” (Universal Declaration of Human Rights) ሲያውጅና ከአስራ ስምንት ዓመታት የጦፈ ክርክር በኋላ
ደግሞ ሰፋ ባለ መልኩ የሰው ልጆችን መብት ጥበቃን ያካተቱትን ሁለቱን ውሎች (Covenants) ሲያጸድቅ፣ መንግሥታት፣
በተለይም የሁለተኛው የዓለም ጦርነት በሰው ልጆች ላይ ያደረሰውን ጥፋት በቅርብ ያዩትና ከሩቅም ሆነው የሰሙት፣ ከልባቸው
የሰው ልጆች ሰብዓዊ መብቶች ካሁን በኋላ እንዳይጣሱ ታሪካዊ ግዴታችንን እናሟላለን ብለው ተስማሙ። እነዚህ የተመድ
መግለጫዎችና ውሎች ከሞላ ጎደል ሁሉም መንግሥታት የተስማሙበትና የፈረሙት፣ የውሎቹንም ጽንሰ ሃሳቦች በየህገ
መንግሥታቸው ውስጥ ያካተቱ ቢሆንም፣ እንደ ኢትዮጵያ ያሉት መንግሥታት ግን አፈጻፀሙ ላይ ወገቤን እያሉ ነው። አገራችን
አብዛኞቹን ዓለም ዓቀፋዊ ውሎችን የፈረመች ቢሆንም፣ እየተከሰተ ያለውን የጅምላ የዜጎችን ሰብዓዊ መብቶች ጥሰት
ስንመለከት፣ ባለሥልጣኖቻችን ዉሎችን መፈረሟንና ያለባቸውን የሰብዓዊ መብቶችን የማስከበር ግዴታ ቅንጣት ታህል
ግንዛቤ ያላቸውም አይመስልም።
ሰብዓዊ መብቶች የሰው ልጆች ብቻ ስለሆኑ መንግሥት የአገር ልዕልናን ለማስከበር ህጋዊ መብት እንጂ፣ ሰብአዊ መብት ብሎ
ነገር የለውም። በምድራችን ላይ የሰው ልጆችን ሰብዓዊና ህጋዊ መብቶችን ሙሉ በሙሉ የማይጥስ መንግሥት አለ ለማለት
አያስደፍርም፣ ሁሉም መንግሥታት መብት ይጥሳሉ ለማለት ይቻላል፥ ልዩነቱ ግን ዲሞክራቲክ መንግሥታት አውቀውም ሆነ
ፀሃፊው ቀድሞ የተባበሩት መንግሥት ባለሥልጣን የነበሩ የዓለም አቀፍ ሕግ ባለሙያ ናቸው።
ሳያውቁ የዜጎችን ሰብዓዊ መብቶችን ሲጥሱ ወይም መብት ጣሾቹን ለፍርድ ካላቀረቡ ተጠያቂ የሚሆኑበት አሰራርና ልምድ
አላቸው። መብቶች ይጣሳሉ፣ መብታቸው የተጣሰባቸው ዜጎች ግን የተጣሰውን መብታቸውን መልሰው የሚያስከብሩበትና
የጣሱባቸውንም ግለ ሰቦች የሚያርም ህጋዊ ደንብና ሥርዓት አለ ማለት ነው። መሰረታዊው በህዝብና በመንግሥት መካከል
ያለው የማህበረሰቡ ውል (social contract) የሚያዝዘው፣ መንግሥት የዜጎችን ሰብዓዊ መብት በመጣስ (action) ብቻ
ሳይሆን፣ እነዚህ መብቶች በሌሎች ሲጣሱ የእርምት እርምጃ ባለመውሰዱም (omission) እኩል ተጠያቂ መሆኑን ነው። በሌላ
አነጋገር፣ የመንግሥት ድርሻ፣ ሰብዓዊ መብቶችን ማክበር፣ ማስከበርና ማዳበር ብቻ ነው።
ባገራችን የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት እንደ ኢህአዴግ ዘመን አስከፊ ደረጃ ላይ የደረሰበት ጊዜ አልነበረም፣ በንጉሱ ዘመን
የፖሊቲካ ሥልጣን ሁሉ በሳቸውና ባካባቢያቸው በነበሩ ጥቂት ቡድኖች እጅ ቢሆንም፣ ህዝቡ የንጉሱን “ሥዩመ
እግዚአብሄርነትንና” የተሾመው ሁሉ የመጨቆን መብት እንዳለው ሳይወድ በግድ “አምኖ” ስለተቀበለ፣ ፊደል ከቆጠሩና
ካንዳንድ “ሽፍቶች” በስተቀር፣ መብቴን ተገፍፌያለሁ ብሎ የሚሞግት ተቃዋሚ ባለመኖሩ፣ የኢትዮጵያ እስር ቤቶች
እንደዛሬው የዜጎች የጅምላ ማሰቃያ ገሃነም አልነበሩም። ተቃውሞውን የሚመሩ ተማሪዎችም በፖሊስ ከተያዙ ወደ ሰንዳፋ
አባ ዲና ፖሊስ ኮሌጅ ተወስደው ከበድ ያለ ስፖርት ያሰሯቸው እንደሁ እንጂ እንደ ዛሬ በሽብርተኝነት ወንጀል ተከስሰው
ረጅም ቅጣት አይፈረድባቸውም። በታሪካችን ውስጥ የሰውን ልጅ ማሰቃየት (torture) የጀመረው ደርግ ቢሆንም ኢህአዴግ
ግን ደርግ እንደ ጀማሪ የተለማመደበትን ሙያ ወደ ኤክስፔርት ደረጃ አሻሽሎና በሰለጠነ መልኩ ሰፋ አድርጎ ዜጎችን ማሰቃየት
ብቻ ሳይሆን “አሰቃይ” የሚል የሙያ ዘርፍ ፈጥሮ “አሰቃዮችን” በዚህ ሙያ አሰልጥኖና ማሰቃያ ማዕከልም ፈጥሮ የዜጎችን
ሰብዓዊ መብት በሰፊው መጣስ የጀመረው።
የኢህአዴግ የዜጎችን መብት የመጣስ ብቻ ሳይሆን፣ ከጣሰም በኋላ ቅስምን የመስበር ባህል ከየት እንደመጣ በጣም ግራ
የሚያጋባ ነው። አዎ! ከልጅነታችን ጀምሮ ወላጆቻችን፣ ደብድቦና አሽንፎ መምጣት እንጂ ተደብድቦና ተሸንፎ መምጣት
“አሳፋሪ” መሆኑን ቢያስተምሩንም፣ ቢያንስ ቢያንስ እኔ ያደግሁበትና ለዘመናት ሲወርድ ሲዋረድ የነበረው ባህላችን፣
በመጀመርያ ደረጃ መታገል ያለብህ በዓቅም ከሚስተካከልህ ጋር ብቻ ሲሆን፣ በለስ ቀንቶህ ታግለህ ተፎካካሪውን ከጣልከው
ግን ደግፈህ ከወደቀበት አንስተህ አቅፈኸው ትንከባከበዋለህ እንጂ በወደቀበት ቦታ ላይ በምንም ተዓምር እጅህን
አታሳርፍበትም። ይህ እንግዲህ ከልጅነታችን ጀምሮ በጭንቅላታችን እንዲሰረጽ ወላጆቻችን ያደርጉ የነበረው ካደግን በኋላ
ከሰዎች ጋር ለሚኖረን ቅራኔ፣ ተቃራኒን ካሸነፍን በኋላ እንድናከብረው ያዘጋጁን ይመስለኛል። የኦሮምኛው ተረት “ጀግና
ባላጋራ የክፉ ቀን አለኝታ ነው” የሚለውም ከዚሁ የመነጨ ይመስለኛል። ዛሬ ዛሬ ግን ነገሮች ሁሉ ተቀያይረው ተፎካካሪን
ማሸነፍ ብቻ አልበቃ ብሎ፣ አስሮና አሰቃይቶ፣ አዋርዶና ቅስም ሰብሮ፣ “ከሰቆቃው ለመገላገል ከፈለግህ ደግሞ ያለ ዓቅሜ
መንግሥትን ተዳፍሬያለሁ” ብለህ ይቅርታ ጠይቅና እፈታሃለሁ የሚል ጠላትን “የማሸነፍ” ብቻ ሳይሆን የመደምሰስ፣ ቅስም
የመስበርና ዳግመኛ እንዳያንሰራራ የሚያደርግ አዲስ የጭካኔ ባህል ባገራችን ሰፈነ።
ያደጉ አገራትና እኛ፣
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ፣ ኢህአዴግ “ተቃዋሚ” የሚላቸውን ለማንበርከክ የተጠቀመው ዘዴ ህገ መንግሥቱን የሚቃረኑ ህጎችን
በማውጣትና በጊዜው ፋሺን የነበረውን የጸረ ሽብር ዓዋጅን የምዕራብ አገሮችን ፈለግ ተከትሎ በማወጅ ነበር። መኮረጁ
ባይከፋም ኢህአዴግ የተሳሳተው ግን በእንግሊዝና በሌሎችም የጸረ ሽብር አዋጅን ባወጁት ዲሞክራቲክ አገራት፣ ዓዋጁ
ከመታወጁ በፊት፣ መሰረታዊ የሆኑት የሰውን ልጅ ሰብዓዊ መብቶች እንዳይጣሱ የሚከላከል ተቋም በህግ ተመስርተው ህዝቡን
እያገለገሉ መሆናቸውን ነው። በሌላ አነጋገር፣ በነዚህ አገራት የጸረ ሽብር አዋጅ በመታወጁ የዜጎች የመናገርና የመጻፍ፣ የማሰብና
የማመን፣ የመሰብሰብና የመወያየት መብቶች በምንም መልኩ አልተሸራረፉም ማለት ነው። መሰረታዊ ሃሳቡ፣ ተቃዋሚ መሆንና
ሽብርተኛ መሆን የተለያዩ ናቸው፣ ተቃዋሚ መሆን ማለት የተለየ አስተሳሰብ ይዞ ላገሪቱ የሚበጅ ከገዢው ፓርቲ የተሻለ
አስተሳሰብ አስተናግዳለሁ ማለት ነው እንጂ ያገሪቷን ህልውና አደጋ ውስጥ እከታለሁ ማለት አይደለም። የፖሊቲካ ሂደት
ደግሞ ፎርሙላ ስለሌለው የኔ ሃሳብ ብቻ ትክክለኛ ነው ብሎ መሞገትና ይባስ ብሎም፣ አስተሳሰብህ ያገሪቷን ህልውና አደጋ
ውስጥ ይከታል በማለት የአንድን ቡድን ወይም ግለሰብ መሰረታዊ የሆነ የማሰብን መብት መንፈግ ማለት ወንጀል ነው።
ሰብዓዊ መብቶች ማክበርን በተመለከተ እስካሁን ኢትዮጵያ ካጸደቀቻቸው ህገ መንግሥቶች ሁሉ የኢፌድሪን ህገ መንግሥት
የሚስተካከል የለም። በህገ መንግሥቱ ከተካተቱት 106 አንቀጾች ውስጥ 32ቱ የሰው ልጆችን ሰብዓዊ መብቶች ጥበቃን
የሚደነግጉ ስለሆነ፣ ይህ ህገ መንግሥት ከሌላ ከማንኛውም ዴሞክራሲያዊ አገር ህገ መንግሥት ጋር በእኩልነት ሊቀርብ
የሚችል ህጋዊ ሰነድ ነው ማለት ይቻላል። አፈጻፀሙን ከዳሰስነው ግን፣ የኢትዮጵያ መንግሥት የዜጎችን መብት በመጣስ
በምድራችን ላይ ከሚጠቀሱ መጥፎ አገሮች ተርታ በመጀመርያ ረድፍ ላይ የሚሰለፍ ነው። ይህ እንዴት ሊሆን ቻለ? አንድ
ድርጅት (ኢህአዴግ) ያን የመሰለ ውብ ህገ መንግሥት መንደፍ ከቻለ ለምንድነው ራሱ ያረቀቀውንና ያጸደቀውን ህገ መንግሥት
በተለይም አከብራቸዋለሁ አስከብራቸዋለሁ ብሎ እየማለ የለፈፈውን የዜጎች መብትን ለማክበር የከበደው? ያ ሁሉ አገሪቷ
ያፈራቻቸው ምርጥ ልጆቿ የተዋጉለትና የሞቱለት የዜጎች ዲሞክራሲያዊና የሰው ልጆች መብት መከበር ጉዳይ እንዴት
በተከታታይ ባላሥጣኖቻችን ተገቢ ትኩረት ሊያገኝ አልቻለም? ለዜጎች የሰው ልጆች መብት ጥሰት ዋነኛ ምክንያት ነበር
የምንለውንና ለዘመናት ሰፍኖ የነበረውን የፊውዳሉን ሥርዓት መሰረቱን ገርስሰን ከጣልን ከአርባ ዓመታት በኋላና በአብዮታዊ
ዲሞክራሲ መሪህ እመራለሁ በሚለው መንግሥት ሥር ዛሬም የዜጎች መብት ጥሰት ጣራ የነካበት ምክንያት ምንድነው?
ለነዚህና ለሌሎች ተጓዳኝ ጥያቄዎች ደርዘን ምክንያቶችን ማቅረብ ቢቻልም፣ እስከ ዛሬ ግን ሳይንሳዊ ጥናቶች ተካሂደውበት
አላየሁም። የዚህ ጽሁፍ ዓላማም ለነዚህ ጥያቄዎች አሳማኝ መልስ ለመስጠት ሳይሆን፣ ነባራዊ ሁኔታውን በጥቂቱ ዳስሼ፣
በመጨረሻ ላይ፣ የዜጎች ሰብዓዊ መብቶች እንዳይጣሱ ይረዳሉ ብዬ የምገምታቸውን፣ በመንግሥትና በዜጎች መወሰድ
ስላለባቸው አንዳንድ እርምጃዎች ለመጠቆም ነው።
የችግሮቻችን ቅርጫት፣
አንደኛው፣ የአገሪቱ ትልቁ ችግር፣ በኔ ግምት፣ የሶስቱ የመንግሥት (State) አካላት “ሥላሴያዊ” ተፈጥሮ ይመስለኛል።
በዲሞክራሲያዊ ሥርዓት በሚተዳደር አገር ሶስቱም የመንግሥት አካላት በውል የተለየ የአሰራር ዘርፍ አላቸው። ህግ አውጪው
(ፓርላማው) ህጎችን ይደነግጋል፣ አስፈፃሚው (የሚንስትሮች ምክር ቤት) ደግሞ ህጎችን በተግባር ይተረጉማቸዋል፣ ዳኝነት
(ዳኞች) ደግሞ ህጎችን ተጠቅመው ላለመግባባቶችና ግጭቶች መፍትሄ ይሰጣሉ ይበይናሉ። የህገ መንግሥቱን ቃልና መንፈስ
በቅንነት ሥራ ላይ ለማዋል ለፈለገ መንግሥት ይህ የሥራ ድርሻ በጣም ግልጽና የማያሻማ በመሆኑ ምንም ዓይነት የአፈጻፀም
ችግር ባላስከተለም ነበር። ባገራችን ግን ሆነ። እንደሚመስለኝ ከሆነ ለዚህ ሁሉ የአፈጻፀም ጉድለት ምንጩ ኢህአዴግ
በፓርላማ ውስጥ መቀመጫውን በሙሉ ስለያዘው፣ በፓርቲና በህግ አውጪው የመንግሥት አካል መካከል መኖር
ያልነበረበትን ግንኙነት ስለፈጠረ ይመስለኛል። በመሆኑም ህጎች የሚረቅቁትና የሚወሰኑት በኢህአዴግ ማዕከላዊ ኮሚቴ ሆኖ
ወደ ህግ አውጭው (ፓርላማ) የሚላኩት “የህዝብ ተወካዮቹ” ዝም ብሎ እጃቸውን እንዲያወጡና እንዲያፀድቁት ብቻ ነው።
ብዙ የፖሊቲካ እስረኞችም በዓደባባይ እንደተናገሩት፣ ዳኞችም ፖሊቲካ እስረኞች ላይ ምን ዓይነት ብይን መስጠት
እንዳለባቸው አስቀድሞ በህወሃት ባላሥልጣን መመርያ ይሰጣቸዋል፤ ይህ የሶስቱ የመንግሥት አካላት ድርሻ በኢህአዴግ
ማዕከላዊነት ዙርያ በመደወሩ፣ የዜጎችን ሰብዓዊ መብቶች ለማስከበር የተፈጠሩ አካላት ማህበረሰባዊ የሥራ ድርሻቸውን
በአግባቡ እንዳይፈጽሙ አድርጓቸዋል። በመሆኑም የዜጎችን ሰብዓዊ መብቶች በአግባቡ እንዲከበሩ ኢህአዴግ ከመንግሥት
አካል ወጥቶ ሶስቱ የመንግሥት አካላት ማህበረሰባዊ ግዴታቸውን ሕጉ በደነገገላቸው መሠረት መወጣት አለበት።
ሁለተኛው የችግራችን ዘርፍ ይህ “መንግሥት” የተባለው ተቋም፣ መብት ሰጪ አካል ሆኖ የመታየቱ ጉዳይ ነው። በመሰረቱ
መንግሥት ማለት የዜጎችን የግልና የቡድን ሰብዓዊ መብቶችን እንዳይጣሱ የመከላከል ግዴታ ያለበት አገልግሎት ሰጪ
ተቀጣሪና የሰው ልጆችን መብት ራሱ በመጣስም (action) ሆነ ሌሎች ሲጥሱት እርምጃ ሳይወስድ ቢቀርም (omission)
በህግ ፊት ተጠያቂ ነው ማለት ነው። ሰብዓዊ መብቶች ለሰው ልጆች ሁሉ ሰው ሆነው በመፈጠራቸው ብቻ እኩል የተሰጣቸው
ስለሆነ መንግሥት እነዚህ ተፈጥሮያዊ መብቶች እንዳይጣሱ ከመንከባከብ ሌላ የራሱ የሆነ ሰብአዊ መብት የለውም። ተከታታይ
መንግሥቶቻችን ግን ይህን መሰረታዊ የሆነ የተፈጥሮ ክስተት በትክክል የተገነዘቡት አይመስልም። ትልቁ ስህተት “መንግሥት”
እና “አገርን” አንድ አድርጎ የማየት ልምድ ነው። በመሆኑም፣ ለምሳሌ የመንግሥትን የሰብዓዊ መብቶች መጣስን ተቃውመው
ዜጎች ለሰልፍ ወጥተው መንግሥቱ ሥልጣን እንዲለቅ ሲጠይቁ፣ “ህገ መንግሥታዊ ሥርዓቱና ያገሪቷ ህልውና አደጋ ላይ
ወድቋል” ይልና የአስቸኳይ ጊዜ ዓዋጅ በማወጅ የዜጎችን ሰብዓዊ መብት ይገድባል። ዕውኔታው ግን አደጋው ያንዣበበው
በመንግሥት ህልውና ላይ እንጂ በህገ መንግሥቱና ባገሪቷ ህልውና ላይ አይደለም። አዎ! የአስቸኳይ ጊዜ ዓዋጅ በማንኛውም
አገር ይታወጃል፣ ግን ከመታወጁ በፊት ቢያንስ ቢያንስ የሚከተሉት ሶስት ቅድመ ሁኔታዎች፣ ማለትም፣ ሀ) የመንግሥቱ
ሳይሆን ያገሪቷ ህልውና አደጋው ላይ መሆኑ፣ ለ) ዓዋጁ ለተወሰነና አጭር ጊዜ ብቻ መሆኑን፣ ሐ) በዓዋጁ ምክንያት መሰረታዊ
የሆኑ የሰብዓዊ መብቶች እንዳይጣሱ ማረጋገጥና ይህንንም ለማስፈፀም ልዩ አካል ማቋቋም የሚሉት መሟላት አለባቸው።
ሶስተኛው ፣የሰው ልጆች ተፈጥሮያዊ ስሜት (natural instinct) የሚባል ነገር ሁሌም እንዳስቸገረ ነው፣ አንድ ግለሰብ፣ በሆነ
ነገር ከሌላው የተሻለ መስሎ ከታየው ራሱን የበላይ አርጎ ማየት ብቻ ሳይሆን ያንን የበላይነት ስሜትን (ጉልበቱን)በተግባር
ለመተርጎም ከኔ ያንሳል ብሎ የሚገምተውን መጨቆንና ማንበርከክ አለበት። የመንግሥት ተፈጥሮም ይህንኑ ያንፀባርቃል።
መንግሥት፣ በተለይም በጠብመንጃ ድጋፍ ሥልጣን ያገኘ ከሆነ፣ መላው የአገሪቷ የኃይል መመዘኛ ተቋም (የመከላከያና
የደህንነት እንዲሁም የፖሊሶችን) በእጁ ስላሉ ብቻ ተጠቅሞባቸው የዜጎችን ሰብዓዊ መብት በመጣስ ጉልበቱን ይፈትሻል።
ከመደበኛው የመከላከያና የደህንነት ኃይል በተጨማሪም እሱን ብቻ ከህዝብ ቁጣና መዓት የሚከላከሉለትን ለምሳሌ በኛ አገር
እንደ አግዓዚ ያሉትን ልዩና ታማኝ ታጣቂ ኃይላትን ያደራጅና የተለየ አስተሳሰብ ያላቸውን ዜጎች፣ “ምን ታመጣለህ”
“አስርሃለሁ” ማለት ይጀምራል። የሥልጣን ወንበሩን፣ አቶ መለስ ይሉ እንደነበረው፣ “ተዋግቼ ሞቼለት ነውና ያገኘሁት አንተም
ተዋጋና ውሰድ” ማለት ይጀምራል። በዚህ አኳኋን መንግሥትም የዜጎችን ሰብዓዊ መብቶች እንዳይጣሱ ከመጠበቅና የህዝብ
ማገልገያ ተቋም መሆኑ ቀርቶ፣ ሆን ብሎ መብቶችን የሚጥስ ፀረ ሕዝብ ተቋም ይሆናል። ባገራችን የዜጎችን ሰብዓዊ መብት
ጥሰት በተመለከተ፣ በኔ ግምት፣ ይህ ትልቁ ምክንያት ይመስለኛል።
አራተኛው፣ በመንግሥት በኩል በሕገ መንግሥቱ ውስጥ መሰረታዊ የሆኑትን ሰብዓዊ መብቶች ዝርዝር ባማረ ቋንቋ ከማካተት
ባሻገር፣ እነዚህን ሕገ መንግሥታዊና መሰረታዊ የሰው ልጆችን መብት በተግባር ለመተርጎም የሚያመች ተቋም ለመመስረትና
ቢመሰረቱም እንዲጎለብቱ አንዳችም ጥረት አልተደረገም። ያደጉ ዲሞክራቲክ አገሮችን የወሰድን እንደሆነ፣ ልጆች ገና ከመዋዕለ
ሕጻናት ጀምሮ ፖሊስ መብታቸውን ለማስከበር የተሰማራ አካል በመሆኑ ወላጆቻቸው እንኳ ካስቀየሟቸው በመጀመርያ ደረጃ
የሚደርሱላቸው ናቸው ብለው የፖሊስን ስልክ ቁጥር በቃል ያስሸመድዷቸዋል። በዚህ መንፈስ ታንጾ ያደገ ልጅ አንድ ቀን
ፖሊስ ለመሆን ከወሰነ፣ በመጀመርያ ደረጃ፣ እንደ ሙያ ግዴታው አድርጎ የሚወስደው የዜጎችን ሰብዓዊ መብት ማስከበር
ነው እንጂ በምንም ተዓምር አንድን ዜጋ “የመንግሥትን ፖሊሲ ተቃርነሃል” ብሎ አስሮ ለመግረፍና ለማሰቃየት አይሆንም።
ባገራችን ግን መንግሥት ሆን ብሎ ፖሊሶችን እስረኛን እንዲያሰቃዩ ልዩ ሥልጠና ይሰጣቸዋል። በመሆኑም ያገራችን ፖሊስ
የየዜጎችን መብት ለማስከበር የቆመ ሳይሆን ለመጣስ የተፈጠረ ስለሆነ ይህንን እያየ የሚያድገውም ወጣቱ ትውልድም የፖሊስና
ደህንነት አባላትን በበጎ ዓይን አይመለከታቸውም። አንድ ቀን ፖሊስ ለመሆን ከወሰነም እሱም የዜጎችን ሰብኣዊ መብት
ለመንከባከብ ሳይሆን የያዘውን ዱላና የለበሰውን ዩኒፎርም ተጠቅሞ የዜጎችን መብት ለመጣስ ይሆናል።
አምስተኛው፣ ሌላኛው ትልቁ የማህበረሰባችን ችግር ደግሞ የባለሥልጣኖቻችን ራሳቸውን ከህግ በላይ አድርገው ማየታቸው
ነው። እስካሁን ድረስ በታሪካችን ሙሉ መሪዎቻችን ሥልጣን ላይ የሚወጡት በጠብመንጃ ድጋፍ ስለሆነ ችግሮችን ሁሉ
ለመፍታት የሚሞክሩት በጠብመንጃ እንጂ ሕግና ሥርዓትን ተደግፈው አይደለም። በጉልበት የተገኘን ሥልጣን ደግሞ ይዞ
ለመቆየት ጉልበት ስለሚያስፈልግ ከባለሥልጣኖቹ የተለየ አስተሳሰብን የሚያስተናግዱ “ተቃዋሚ” ሃይላትን በጉልበት
ለማዳከም እንጂ መሳርያን ያላካተተ ውይይት አድርጎ ማህበረሰባዊ ቀውሶችንና ተጓዳኝ ችግሮችን ለመፍታት አንዳችም ዓይነት
ጥረት አይደረግም። አለመግባባትን ከሥሩ ተወያይተውበት ዘላዊ መፍትሄ ከመፈለግ፣ መፍትሄም ካልተገኘ ደግሞ ልዩነትን
አቻችሎና ባለመስማማት ተስማምቶ አብሮ ለመኖር ሙከራ ከማድረግ ይልቅ፣ “ባንድ ጥይት መገላገል ስችል ወይም ደግሞ
ወህኒ ቤት ወርውሬህ ጸጥ ላሰኝህ ስችል ካንተ ጋር ምን አጨቃጨቀኝ” የሚለውን ችግሮችን የሚያባብስ እንጂ የማይቀርፈውን
የደካሞች የችግር መፍቻ ዘዴ መጠቀምን ይመርጣሉ። በኔ ግምት ባገራችን ትልቁ የሰው ልጆች መብት ረገጣን ካስከተሉ
ድርጊቶች ቀዳሚው ይህ የማን አለብኝነትና በጠብመንጃ ሃይል ችግሮችን ለመፍታት የመሞከር ልምድ ይመስለኛል።
መደረግ ያለባቸው
የሰው ልጆችን መብት ማክበርን በተመለከተ፣ በቅርቡ የተወሰኑ በፌዴራልና በብዙ ሺህ የሚቆጠሩትን ደግሞ ከክልል እስር
ቤቶች የፖሊቲካ እስረኞችን ከመፍታት በተጨማሪ፣ ምናልባትም በታሪካችን ውስጥ ለመጀመርያ ጊዜ፣ የተባበሩት
መንግሥታት ድርጅት የሰው ልጆች መብት ኮሚሽኔርን ለኦፊሴላዊ ጉብኝት መጥራታቸው፣ አንድ ተስፋ ሰጪ አዲስ ምዕራፍ
ነው ቢባል የተጋነነ አይሆንም። ኮሚሽኔሩም በቆይታቸው ጊዜ ጠቅላይ ሚኒስትሩንና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩን ከማነጋገር
በተጨማሪ፣ ከቀድሞ የፖሊቲካ እሥረኞች፣ ከተቃዋሚ ፓርቲዎች መሪዎችና ከአባ ገዳዎች ጋር በግልጽ መወያየታቸው፣
በተመድና በኢትዮጵያ መንግሥት መካከል በአዲስ አበባ የቀጠና ቢሮ ለመክፈት መፈራረማቸው በሰው ልጆች መብት
ተሟጋቾች ዘንድ እንደ ታላቅ ድል ተቆጥሮአል። ጅማሬው ጥሩ ቢሆንም ተግባራዊ የሚያደርግ መንግሥታዊ ውሳኔ
ካልታከለበት በቀር፣ ለዘመናት የተተበተብንበትን የግፍ ድር በቀላሉ በጣጥሰን መንፈሳችንን ነጻ አድርገን በሙሉ ልብ
ለመብታችን እንድንታገልና፣ ስለ ሰው ልጆች መብት ምንነት እንዲሁም፣ የራሳችንንና የመንግሥትን ሚና በትክክል
እንድናውቀው፣ ዘርፈ ብዙ የሆነ ብሄራዊ የሰው ልጆች መብት ጥበቃ የአቅም ግንባታ መርሃ ግብር ማውጣት ቀዳሚ ተግባር
ነው። አገር ማለት ሰው እንጂ ግዑዙ ምድር ስላይደለ፣ ስለ አገራችን ነጻነት፣ ሰላምና መረጋጋት ስናወራ በውስጧ ስለሚኖሩ
መቶ ሚሊዮን ዜጎች መሆኑ ታውቆ፣ ዜጎች መብታቸውን በትክክል እንዲያውቁና እንዲንከባከቡት፣ ሲጣስባቸውም በደንብ
እንዲዋጉለት የሚያስችል ዕውቀትን መሰረት ያደረገ ትልቅ መርሃ ግብር ማውጣት የመንግሥቱ ተቀዳሚ ግዴታ መሆን አለበት።
ይህ የረጅም ጊዜ መርሃ ግብር ሲሆን ባጭር ጊዜ ውስጥ ደግሞ የሚከተሉትን እርምጃዎች ቢወስድ፣ እውነትም ይህኛው
የኢህአዴግ አባል ትውልድ ካንጋፋዎቹ የተለየና ህዝብ ህዝብ የሚሸት፣ የህዝቡ ችግር የተሰማው ነው ብለን መናገር እንችላለን።
ሰብዓዊ መብቶችን የማክበር ባህል በሰው አእምሮ ሰርጾ፣ ዜጎች መብታቸውን በትክክል አውቀው እንዲከባከቡትና
እንዳይጣስባቸውም ለመከላከል የሚረዳቸውንና መደረግ ያለባቸው ነገሮችን በሙሉ መዘርዘር የሚቻል አይመስለኝም። ሆኖም
ግን ዛሬ በዓለማችን ከምናያቻውና ከምናስተውላቸው በመነሳት፣ የዜጎችንና የመንግሥትን የሥራ ድርሻ በጥቂቱ ለመጥቀስ
ያህል ከዚህ የሚከተሉትን ማሳሰቢያዎችን ማስቀመጥ ይቻላል።
ሀ) በመጀመርያ ደረጃ፣ መንግሥት የዜጎችን ሰብዓዊ መብቶች ለማክበር ለማስከበርና ለማዳበር ብቸኛ ተጠያቂ መሆኑን
ጠንቅቆ ማወቅ አለበት። በመሆኑም፣ የዜጎችን ሰብዓዊ መብት በመጣስ የታወቁትን የጸረ ሽብርና የበጎ አድራጎት ድርጅቶች
ዓዋጆችን በአስቸኳይ አሻሽሎ ከሕገ መንግሥቱ ቃልና መንፈስ ጋር ማጣጣም አለበት።
5 | P a g e
ለ) በወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር የዋሉትን ዜጎች ለመጠበቅ ኃላፊነትና ግዴታ የተጣለባቸው ኃይላት፣የዜጎችን ሰብዓዊ
መብት እንዲያከብሩ በማሰልጠኛ ተቋማት ተጠያቂነትን የማስተማር፣ የማሰልጠንና የማዘጋጀት መንግሥት ትልቅ ኃላፊነት
አለበት። ይህንን ኃላፊነት በተጠበቀው ደረጃ ሊወጡ ያልቻሉትን በተለይም በቁጥጥራቸው ሥር በዋሉ ዜጎች ላይ የማሰቃየትና
ተመሳሳይ ሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን በሚፈጽሙ የደህንነትና የፀጥታ አስከባሪ ኃይላት ላይ ደግሞ ባገሪቷ ሕጎችና ደንቦች
በተደነገው መሰረት የማያወላውል እርምጃ መውሰድ አለበት።
ሐ) የዜጎችን ሰብዓዊ መብት መከበርን ለመታዘብና ሲጣስም እርምት እርምጃ እንዲወስድ ሙሉ ኃላፊነት ያለው፣ ተጠያቂነቱም
ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ብቻ የሆነና የሕዝብ አመኔታ ያለው የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽኔር ተቋም ማቋቋም ያስፈልጋል።
የኮሚሽኔሩ ቢሮ ከማንም ጣልቃ ገብነት ነጻ እንዲሆንና ተጠያቂነቱን ለፓርላማው ብቻ ማድረግ፣ እንዲሁም ያላንዳች መሰናክል
በፈለገበት ሰዓት እሥር ቤቶችን ለመጎብኘትና ለመገምገም፣ የፍርድ ቤቶችንም ሂደት ለመከታተል የሚችል በየክፍለ አገሩም
ቅርንጫፍ ቢሮዎችን መክፈት የሚችል ጠንካራ ተቋም መሆን አለበት።
መ) ዜጎች በሕገ መንግሥቱ የተረጋገጠላቸውን ሰብዓዊ መብቶችን በተለይም የመናገርና የመጻፍ መብታቸውን በተግባር
እንዲተረጎም ከተፈለገ፣ መንግሥት የሚዲያ ሕጎችን ከህገ መንግሥቱ ቃልና መንፈስ ጋር በሚጣጣም መልኩ ማሻሻል አለበት።
በመጀመርያ ደረጃ ይህ “የመንግሥት ሚዲያ” የሚባለው የተሳሳተ ልምድ መቆም አለበት። መንግሥት የራሱ የሆነ ሚድያ
ሊኖረው አይገባም፣ ሚድያ የሕዝብ ነው፣ ስለሆነም ማንኛውም ዜጋ ያላንዳች አድልዖ በእኩልነት ሊጠቀምበት ይገባል እንጂ፣
መንግሥት ልክ የራሱ ንብረት አድርጎት ሌሎች ከሱ ጋር በአስተሳሰብ የማይግባቡትን ግን “ተቃዋሚዎች ስለሆኑ በመንግሥት
ሚድያ መጠቀም አይችሉም” ብሎ ማግለል የዜጎችን ሰብዓዊ መብት መጣስ ነው። ገዢው ፓርቲ ከፈለገ በአባላቱ ድጋፍና
መዋጮ የራሱን ቲቪና ሬድዮ ጣቢያ ያቋቋማል እንጂ፣ ዜጎች በሚከፍሉት ግብር የሚንቀሳቀሰውን ቲቪና ሬድዮ እንደ ራሱ
ንብረት መቁጠር ሥልጣንን ያላግባብ መጠቀምና ብሎም የዜጎችን መብት መጣስ ነው። በመሆኑም፣ መንግሥት ይህንን ጸረ
ሕገ መንግሥታዊ አሰራር አቁሞ፣ ሚድያው ያላንዳች አድልዖ ዜጎችን በሙሉ በእኩልነት የሚያስተናግድ መሆኑን ማረጋገጥ
አለበት።
ሠ) ሰብዓዊ መብቶችን የማክበር የረጅም ዘመን ልምድ ካላቸው ወዳጅ አገራትና ዓለም ዓቀፋዊ የሰው ልጅ መብት ተሟጋች
ድርጅቶች ጋር በመተባበር፣ ባገራችን የሰብዓዊ መብቶችን የማክበር ባህል እንዲዳብር መንግሥት አስፈላጊ ትኩረት ማድረግ
አለበት። የሰብዓዊ መብቶች መከበር መሰረታዊ የሆነና ከልጅነት ጀምሮ በዜጎች አዕምሮ መሰረጽ ያለበት ስለሆነ መንግሥት
ለዚህ ተገቢ ትኩረት ሰጥቶ ያገሪቷን የማስተማርያ ካሪኩለም ማሻሻል አለበት። ወጣቱን ትውልድ ሰብዓዊ መብቶችን በማክበር
ባህል ታንጾ እንዲያድግ ከሚደረገው መርሃ ግብር አኳያ፣ በፖሊስ ማሰልጠኛዎች ተቋም ውስጥ፣ ህገ መንግሥቱን መሰረት
ያደረገና ጥልቅ የሆነ የሰብዓዊ መብቶች አከባበር ትምህርት፣ እንዲሁም የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነትና ተጠያቂነት ማስተማር
መንግሥት መወጣት ካለባቸው ግዴታዎች ቀዳሚው መሆን አለበት።
ረ) ሌላው ለሰብዓዊ መብቶች ጥሰት በሚያሳዝን መልኩ አሉታዊ ሚና በመጫወት ላይ ያሉት የሕግ ባላሙያዎች ማለትም
የዓቃቤ ህጎች፣ የጠበቆችና የዳኞች ተግባር ነው። በመጀመርያ ደረጃ፣ ዓቃቤ ህግ ወይም ዳኛ ሆኖ ለመሾም ለገዢውን ፓርቲ
ታማኝነትን ይጠይቃል። ዳኝነት ግን ከሕክምና ባላነሰ መልኩ የብዙ ዓመታት ልምድን እንጂ በታማኝነት ብቻ የታለመለትን
ግብ የማይመታ በመሆኑ፣ እነዚህ ወጣት ዳኞች ከልምድ ጉድለትና በመንግሥት ጫና ምክንያት ፍትህን ሊያገለግሉ
ባላመቻላቸው፣ ዓቃቤ ህጉ “ከመንግሥት የተለየ አስተሳሰብ በማስተናገዳቸው ብቻ” የወንጀል ክስ የሚመሰርትባቸውን ዜጎች
ፍትሃዊ ያልሆነ ውሳኔ ያስተላልፉባቸዋል። ስለዚህ መንግሥት በርግጥም የዜጎችን ሰብዓዊ መብት የማስከበር ግዴታውን
በአግባቡ ለመወጣት ይችል ዘንድ ከፈለገ፣ በዳኝነት ሙያ ላይ የሚሰማሩ የህግ ባለሙያዎች የሚሾሙት ለገዥው ፓርቲ
ባላቸው ታማኝነት ሳይሆን፣ ከማንኛውም ተጽዕኖ ነጻ የሆኑና ይህንን ነጻነታቸውን በረጅም የአገልግሎት ዘመናቸው ያስመሰከሩ
ግለሰቦች መሆን እንዳለባቸው መንግሥት አምኖ መቀበልና ይህንንም ለማስተካከል አስፈላጊውን እርምጃ መውሰድ አለበት።
እኛ ማድረግ ያለብን፣
ሀ) ሰብዓዊ መብቶች እንዳይጣሱ ትልቁ የመከላከያ ጋሻ ዜጎች ስለ መብቶቻቸው ያላቸው የእውቀትና የንቃት ደረጃ ነው።
የመንግሥት የጸጥታና የመከላከያ ኃይል የፈለገውን ያህል ጠንካራና የተደራጀ ቢሆንም፣ ለመብቱ በቂ ዕውቀት ያለውንና
መብቱን ከጥሰት ተከላክሎ ለማዳን የነቃውን ሕዝብ ሊያሸንፍ የሚችል ምድራዊ ኃይል ሊኖር አይችልም። ስለዚህ የኛ የዜጎች
ትልቁ ሚና መሆን ያለበት መጀመርያ ስለራሳችን መብት ያለንን ዕውቀት ማበልፀግና ይህንንም ብልፅግና በአግባቡ በዜጎች
አዕምሮ እንዲሰርጽና ሕዝቡ ለራሱ መብት ዘብ እንዲቆም ማስተማር ቀዳሚው የዜግነት ግዴታችን ይመስለኛል። አዎ!
ለማስተማር ደግሞ አስቀድሞ መማር ያስፈልጋልና፣ በእልህ ተገፋፍተን ዜጎችን ለበቀል እርምጃ ከመገፋፋት ተቆጥበን፣ ራሳችን
በሕግ የበላይነት ባሕል መስፈን አምነን መቀበልና ይህንንም እምነት ላልተማረው ወገናችን ባግባቡ ማስተለፍ አለብን።
ለ) በዚሁ ልክ ማስተማር ያለብን ትልቅ ቁም ነገር ደግሞ፣ ማንኛውም ዜጋ የሌላው ዜጋ ሰብዓዊ መብት ሲጣስ አይቶ ዝም
እንዳይልና ያንደኛው መብት ሲጣስ ልክ የራሱ መብት እንደተጣስ እኩል እንዲሰማው ነው። የዜጎች ሰብዓዊ መብት ሲጣስ
እያየን፣ የተቃውሞ ድምጻችንን ከማሰማት መቆጠብ፣ የወንጀሉ ተባባሪ መሆን ነው። በመንግሥታት ደረጃ፣ በሌላ አገር የውስጥ
ጉዳይ ጣልቃ አንገባም እየተባለ ሰብዓዊ መብቶች ሲጣሱ ዝም ብሎ የማየት ጊዜው እንዳለፈበት ሁሉ እኛም ዜጎች የሌላ ዜጋ
መብት ሲጣስ ካየን ድምፃችንን ማሰማት አለብን። ዛሬ በኢትዮጵያ ውስጥ ለሚፈጸመው የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ሜክሲኮ
ወይም ሲድኒ ያለው የሰው ልጆች መብት ተሟጋች ቡድን ወይም ድርጅት የኢትዮጵያን መንግሥት በመብቶች ጥሰት ወንጀል
በተመድ ወይም ዓለም ዓቀፉ የወንጀል ችሎት ላይ የመክሰስ መብት አለው። የቺሌውን ፒኖሼን እንግሊዝ ላይ ያሳሰረው
ወይም የቻዱን ሃብሬ በዓለም ዓቀፉ ችሎት ፊት እንዲቀርብ ያደረገው ተቀማጭነቱ ኒው ዮርክ የሆነው የሁማን ራይትስ ዎች
ነበር። ስለዚህ የዜጎቻችን ሰብዓዊ መብቶች ሲጣሱ ከኛም አልፎ የሌሎች አገር ዜጎችና የሰው ልጆች መብት ተሟጋቾች
እንዲሰማቸው ቅስቀሳ ማድረግ ታሪካዊ ኃላፊነታችን መሆን አለበት።
ሐ) በኢህአዴግ ዘመነ መንግሥት በዜጎቻችን ላይ የተፈጸመው የመብት ጥሰት እጅግ ዘግናኝ በመሆኑና ግፉ ደግሞ
የያንዳንዳችንን ቤት ስላንኳካ፣ ይህ መንግሥት በአስቸኳይ እንዲወድቅና የዜጎችን መብት የጣሱ ባላሥልጣናትም ለፍርድ
እንዲቀርቡ ከልብ እንመኛለን። ትክክለኛ ምኞት ነው። ሆኖም ግን በእልህ ተነሳስተን፣ ፍትህን ያለፍርድ ሂደት ራሳችን ሥራ
ላይ እንዳናውላት እፈራለሁ። እኛም ኢህአዴግን የምንከስበትን ጸረ ሕገ መንግሥታዊ አሰራር ደግመን እንዳንሰራ መጠንቀቅ
አለብን። ፍትህ ይዋል ይደር እንጂ የበላይነቱን ያሳያል። የሰብዓዊ መብት ጥሰት ወንጀል ደግሞ እንደ ሌሎች ወንጀሎች የይርጋ
ዘመን ስለሌለው፣ ወንጀለኞቹ በዚች ምድር ላይ እስካሉ ድረስ ከየትም ቢሆን ታድነው መጥተው ለፍርድ መቅረባቸው አይቀሬ
ነውና፣ ዛሬውኑ መብት ጣሶቹ ካልተሰቀሉ በማለት በዝግታ እየሄደ ያለውን ጥገናዊ ለውጥ መስመር እንዳናስትና ህብረተሰቡን
ለብቀላና ማለቂያ ለሌለው ተጓዳኝ ግጭት ከሚያዘጋጅ ቅስቀሳና እንቅስቃሴ ብንቆጠብ የተሻለ ይመስለኛል።
ጄኔቫ፣ ግንቦት 18 ቀን 2018 ዓ/ም
wakwoya2016@gmail.com